434
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ መሰረት በመጪዎቹ የበአል ቀናት ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደማቅ አቀባበል ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነዉ።
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳዉ በአቀባበሉ በባህል ቱሪዝም ዘርፍ እየተሰራ ያለዉን የቅድመ ዝግጅት ስራ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው፥ በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን እዉነት ለአለም በማሳወቅና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን በመቀልበስ፣ የበቃ ዘመቻን በመቀላቀልና ውጤታማ ስራ በመስራት የህልውና ዘመቻ ግንባሩን በድል የተወጡ ዳያስፖራ ጀግኖቻችንን ስንቀበል የከተማው ነዋሪ ለነዚህ ጀግኖች የአገር ልጆች አክብሮት በመስጠትና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ለዚህም በመጪዎቹ የበአል ቀናት ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ከ1 ሚሊየን በላይ ዳያስፖራዎች አቀባበል ከቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አንስቶ በሆቴሎች፣ በትራንስፖርት አቅራቢዎች፣ በጉብኝት ስፍራዎች ለዚህ ክብረበዓል በተለየ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች፣ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች እስከ 30 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም በመግለጫው ተናግረዋል።
ወደ አገር ቤት እንደሚመጣ ከሚጠበቀው ከፍተኛ ቁጥር አንፃር የሆቴሎች የመኝታ አቅርቦት አለመመጣጠን ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ የእንግዳ ማረፊያ፣ አፓርትመንት ያላቸው ግለሰቦች በሚኖሩበት ክፍለ ከተማ የባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ተቋም በመሄድ ጀግኖች እንግዶቻችንን በተገቢ መንገድ ማስተናገድ እንዲቻል ተገቢና ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋ በመተመን እንዲያሳዉቁና ለመኝታ አገልግሎት ምቹ የማድረግ ስራ ከወዲሁ እንዲጀምሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
Source: FBC