ታህሳስ 11፣ 2014 – የዓለም አቀፍ ኢትዮጵያውያን የተባበረ ዳያስፖራ ጥምረት ከ1 ሚሊዮን ወደ ሀገር ቤት የጉዞ መርኃ ግብር በፊት ከኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች 100 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ወጥኛለሁ አለ።
ሀገራዊ ጥሪውን የተቀበለ ማንኛውም ዳያስፖራ ወደ ሀገር ቤት ቢሄድም፣ ባይሄድም ከአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ በነፍስ ወከፍ 100 ዶላር በመቀበል፣ 100 ሚሊዮን ዶላር ከጉዞው በፊት ለመሰብሰብ ማሰቡን ሰምተናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በአገር ቤት በሚዘጋጁ የፈንድ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሮች፣ 400 ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ውጥን መኖሩን ጥምረቱ ለሸገር ከላከው መግለጫ ተመልክተናል።
ገቢው ከመንግሥት ጋር በመተባበርና በውጭ ከሚገኙ የዳያስፓራ ማኅበራት ጋር በመቀናጀት ይሰበሰባል መባሉንም ከመግለጫው ተረድተናል።
የጉዞው ዓላማና ግብ 500 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብን ያካትታል ተብሏል።
ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያውያን የተባበረ ዳያስፖራ ጥምረት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለመመከትና በምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን የሚሰራጨውን የተሳሳተ ቅስቀሳ እንደሚፋለም ተናግሯል።
ማኅበሩ ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት፣ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያደርግ ዲጅታል ዲፕሎማሲን እና ሰላማዊ ሰልፎችን በማዘጋጀት የበረታ ሥራ እየከወነ መሆኑን ተናግሯል።
በአሜሪካ ግንባር ቀደም አስተባባሪነት ምዕራባውያን ኃይሎች፣ እንደ CNN፣ ሮይተርስ፣ BBC እና አሶሺዬትድ ፕሬስ ያሉ መገናኛ ብዙኃንን ተጠቅመው የከፈቱትን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለማክሸፍና ለማምከን እየሠራ መሆኑን ማኅበሩ ተናግሯል።
ማኅበሩ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመመከት፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ከፍ ለማድረግ፣ የዲያስፖራ ቱሪዝምን ለማበረታታት እንዲሁም ለመከላከያ ሠራዊት ደም ለመለገስ እንደሚሠራ ከላከልን መግለጫ ተመልክተናል።
ተህቦ ንጉሴ